1. Elias Gebru
  2. ወጎችና መጣጥፎች / Creative Articles
  3. Sunday, 14 May 2017
ፍቅር በወረፋ . . .
ካስትሮ ከካምፓስ ‹ቤስት ፍሬንዶቼ› አንዱ ነው፡፡ከፍሬሽ ጀምሮ ስለ ፊደል ካስትሮ አውርቶ ስለማይጠገብ ካስትሮ የራሱ ስም ሆኖ ቀረ፡፡ ከዛሬ 3 ሳምንታት በፊት ይሆናል ፊቱን ክስክስ አድርጎት መጥቶ በምሬት ድምጽ፡
ʽʽኧረ ኤላ የዘንድሮ ቺኮች የመጨረሻ አዛ ናቸው” ያለኝ፣ የካስትሮነቱ ሌላው መገለጫ የሆነውን ፂሙን በንዴት እያጉተለተለ
ʽʽ ምነው? ምን ሆንክ ደግሞ?ʼʼ ወሬው አጓግቶኛል!
ʽʽባክህ የሆነች ‹በርድ› ልጅ ባለፈው ተዋውቄ ነበር አላልኩህም?ʼʼ
ʽʽ ትዝ ይለኛል፤ እና ምን ተፈጠረ?ʼʼ
ʽʽስልህ በጣም ተመችታኝ… የሆነ ፎንቃ ነገር ጠለፈኝ መሰለኝ…ʼʼ
ʽʽመሰለኝ ማለት? ʼʼ… ፍቅር ይዞኛል ሲል ዛሬ ገና ሰማሁት፡፡
ʽʽከትላንት ወዲያ አገኘኋትና እንደወደድኳት ምናምን ልነግራት ስሞክር . . .፤ወይኔ! እንዴት እንደሳቀችብኝ አትጠይቀኝʼ
ʽʽየምርህን ነው?ʼʼ
ʽʽአዎዋ! ምን እንዳለችኝ ታውቃለህ? … ያውም እያላገጠች፤ ʽአንተ ሼም አይዝህም እንዴ? በዚህ በግሎባላይዜሽን ዘመን ወደድኩሽ ምናምን ስትል? በአሁኑ ጊዜ እኮ ፍቅር የጌጃዎች ነው፡፡ ባይገርምህ እኔ ፍቅርን የማውቀው ሮማንቲክ ፊልሞች ላይ ብቻ ነው ፡፡ ባይሆን ወደ ማታ ደውልልኝና ፈታ ማለት እንችላለን”
ʽʽ እና ደወልክላት ?ʼʼ አላስጨረስኩትም
ʽʽ ምን ጥያቄ አለው! ጌጃ መሰልኩህ እንዴ? ደውዬ ማታ አገኘኋት እና ʽሸራ ተጓተትንʼ፡፡ በንጋታው ስደውል ግን ለኔ ደንታም ሳትሰጥ ከሌላ ወንድ ጋር እርቃንነት የቀረው ወሲብ ስታደርግ አየኋት” አለኝ በንዴት
እየተንቦገቦገ እኔ ጋር የመጣው ለዚህ ኖሯል፤ ንዴቱ ሲያበግነው ሳይ አንጀቴን በላኝ…
ክስተቱን ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ ይህ የብዙሀኑ የጊቢ ተማሪ ነባራዊ እውነታ መሆኑ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ካምፓሶች ወንድና ሴቶች በነጻነት የሚገናኙባቸው ዋነኛ ስፍራቸው ናቸው፡፡
ገና ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ፍቅር እየተጀመረ ቢሆንም ካምፓስና ኮሌጅ ግን ይገዝፋል፡፡
የካምፓስ ጠበሳ ጥንስሱ የተለያየ ቦታ ቢሆንም “ስልክ” የሚባል የጋራ መዳረሻ ግን አለው፡፡
ʽሄሎ . . .ሄሎ. . .እንዴት ነሽ?ʼ ተብሎ 3 ሰዓት የተጀመረው ወሬ በቴሌ ኔትወርክ ምቀኝነት ወይ በካርድ ማለቅ ካልተቋረጠ እስከ እኩለ ሌሊት ይቀጥላል፡፡ አንዳንዶቹማ ሱስ ሆኖባቸው በየቀኑ ሞባይላቸውን ከጆሮአቸው ለጥፈው ʽʽሹ. . .ሹ. . .ሹʼʼ ካላሉ እንቅልፍ የለችም!
የስልክ ጅንጀና ዋናው ችግሩ የካርዷ ነገር ነች፤ በ5 እና 15 መሀል እየዋዠቀ በየቀኑ የሚሞላው ካርድ በወር ስንት እንደሚመጣ ምቱት… ከባድ ኢንቨስትመንት ነው፡፡
እና እላችኋለው ወንዱ በስልክ ይጀነጅን፤ ይጀነጅን… እና በአካል ለመገናኘት እድል ይሰጠዋል፡፡ አቅሙ ያለው እራት ምናምን ይጋብዛል፡፡ የሌለው ወይም መውጣት ያልፈለገ ደግሞ በጊቢ ውስጥ ተማሪና የጥበቃ ፖሊሶች በማይበዙባቸው ጨለም ጨለም ያሉ ቦታዎች ወይም ‹የጅንጀና እስፖቶች› ተፍተፉን ይቀጥላል፡፡ በጊዜ ሂደትም መደባበሱ ፤መተቃቀፍ ና መሳሳሙ ይጀምራል፡፡ የተወሰኑት እውነተኛ ፍቅርና ማስተዋልን ተመስርተው ይደረጋሉ፡፡
በውሸትና በማስመሰል ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ግን ዘላቂነት አይኖረውም፡፡ መተማመንን እንደ ሃላፊነታቸው ያልተቀበሉ ተማሪዎች በፍቅር ስም በጊዚያዊ ፌሽታ ሙድ ይስታሉ፡፡
በስልክ እና ቻት/‘chat’ በኩል ብጀምር፤ ወንድየው ‹እወድሻለው ደህና እደሪልኝ› ብሎ ስልኩን ይዘጋና ሌላዋ ሴት ጋር ደውሎ መጀናጀን ይጀምራል፤ እሷስ ምኗ ሞኝ ነው! ልክ የሱ ስልክ እንደዘጋ ‘call waiting’ ላይ ይጠብቋት ከነበሩ ወንዶች መካከል ከአንዱ ጋር ጅንጀናዋን ትቀጥላለች፡፡ የውሸት -ʽእወድሀለውʼ -ʽናፍቀሽኛል ʼ በምላስ ይሞሸራል፤ ʽI love youʼ ተብሎ በ ‘chat’ በአንዴ ለብዙ ‹online› ተጀናጃኞች ይላካል፤ ‹ፍቅር በወረፋ› ይብጠለጠላል፡፡
እነዚህ ዓይነቶቹን ወረተኛ አፍቃሪዎች፣ ተማሪዉ ፕሌየርስ (players) ይላቸዋል፡፡ በፍቅር የሚጫወቱ እንደማለት ነው፡፡
ለአባላዘር በሽታ ተጋላጭነቱ እንዳለ ሆኖ አፍቅሮ በማጣትና መካድ ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ትምህርትን እስከ ማቋረጥ ፣የአእምሮ ህመምተኛ እስከ መሆን ብሎም ራስን የማጥፋት ሙከራ እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡ አልባትም ጓደኛዬ ካስትሮ በፍቅር ላይ ተስፋ ከቆረጡ ሰዎች አንዱ ሆኖ ይሆናል፡፡
ይህን ፅሑፍ እየፃፍኩኝ “ካስቴ በእውነተኛ ፍቅር ታምናለህ?” ስል አለሳልሼ ጠየኩት፤ እሱ ግን በምፀት ሳቀና ወረደብኝ፡፡
ʽʽዝም ብለህ ነው ምታልመው፤ የጌጃዎቹ ማግኔት እየሳበህ ነው መሰለኝ፤ እስኪ ለአፍታ ዙሪያህን በደንብ ተመልከት! ፍቅር ይታይሃል? ተማሪው እኮ በጎሪጥ ነው የሚተያየው፡፡ ኩራት፣ ንቀትና አጉል ስልጣኔ ልቦናውን ወርሶታል፡፡ ይልቅ ልምከርህ በአሁኑ ወቅት በውሸት እና ማስመሰል ውስጥ ስትኖር ‹አራዳ›፤ በፍቅር እና የዋህነት ስትኖር ግን ‹ፋራ› ነህ፡፡ʼʼ አንገቴን ወደ መሬት ደፍቼ ከመስማት በስተቀር ምንም መልስ አልሰጠሁትም፡፡ውስጤ ግን አንድ ጥያቄ ደጋግሞ እየጠየቀኝ ነበር-- ʽʽ እውነት ፍቅር የፋራ ነው?ʼʼ
የእናንተን መልስ ባላውቅም ለኔ ግን ፍቅር የፋራም የአራዳም አይደለም፣ የፈጣሪ እንጂ !!

(ይህ ተሻሽሎ የቀረበ ፅሁፍ በመጀመሪያ በ‹ዳና› መፅሄት የሚያዚያ 2007 እትም ስር ‹ፍቅር በወረፋ› በሚል ርዕስ ታትሞ የወጣ ሲሆን ቀጥሎም “ኮሜንት” ከተሰኘው መፅሐፍ ላይ ተካቷል፡፡)
Comment
There are no comments made yet.


There are no replies made for this post yet.
Be one of the first to reply to this post!