1. denberu erdia
  2. ዳሰሳዊ ፅሁፎች / Featured Articles
  3. Tuesday, 09 May 2017
በታዋቂ ክሊኒኮች በራፍ ላይ ደንበኛ ፍለጋ የሚታትሩ ደላሎች አሉ

ትምህርቷን አቋርጣ የትውልድ መንደሯን ጥላ በስደት አዲስ አበባ እንድትመጣ ያስገደዳት ሳይታሰብ ድንገት የተፈጠረ እርግዝና ነው፡፡ ተወልዳ ባደገችበት ደብረብርሃን ከተማ፣ አብሯት ካደገው የልጅነት ጓደኛዋ ጋር ፍቅር የጀመሩት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነበር፡፡
ግንኙነታቸው ከጓደኝነትና ከከንፈር ወዳጅነት አልፎ አንሶላ ለመጋፈፍ ሲያበቃቸው ዕድሜያቸው ገና በአስራዎቹ መጨረሻ አካባቢ ላይ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መማር በጀመሩ ጥቂት ወራት ውስጥ በድብቅ የፈፀሙትን የፍቅር ግንኙነት ገሃድ የሚያወጣ ድንገተኛ ነገር ተከሰተ፡፡
የአስራ ስድስት ዓመቷ ሰናይት /ለዚህ ፅሁፍ ስሟ የተቀየረ/ በዕድሜ 3 ዓመት ከሚበልጣት የልጅነት ፍቅረኛዋ ማርገዟን አወቀች፡፡ ሁኔታው እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ሰማይ ምድሩ ዞረባት። የትውልድ አካባቢዋ ከጋብቻ በፊት የሚከሰት እርግዝናን አጥብቆ የሚጠላና የሚጠየፍ መሆኑን ጠንቅቃ ስለምታውቅ፣ እርግዝናዋ ሶስተኛ ወሩን ከማስቆጠሩ በፊት ከወላጆቿ ቤት ጠፍታ በሆዷ የያዘችውን ፅንስ የሚያስወርዱ ክሊኒኮች በብዛት አሉ ወደተባለችበት ከተማ፣ ጨርቄን ማቄን ሳትል ከቤቷ ጠፍታ አዲስ አበባ ገባች፡፡
ለንግድ ሥራ ጉዳይ ደብረብርሃን ሲመላለሱ ከምታወቃቸው አንዲት አረቄ ነጋዴ ሴት ቤት በእንግድነት አርፋ፣ በሆዷ የያዘችውን ፅንስ የሚያስወጡ ሰዎች ፍለጋ ያዘች፡፡ በሰው በሰው አጠያይቃ፣ ካቴድራል ት/ቤት አካባቢ አለ ተብሎ ወደተነገራት ክሊኒክ አመራች፤ ቦታው ደርሳ የክሊኒኩ መግቢያ ግር ቢላት ከመንገድ ዳር ያገኘችውን ሊስትሮ ጠየቀችው፡፡ ክሊኒኩ መዘጋቱንና የፈለገችውን አገልግሎት በአነስተኛ ዋጋ ሊሰጧት የሚችሉ ‹‹ሐኪሞች›› በአቅራቢያው እንደምታገኝ ነግሮ፣ እየመራ ወደ አንድ ግቢ ይዟት ሄደ፡፡ ነጭ ጋዋን ለብሶ ደንበኞቹን እየተቀበለ የሚያስተናግደው “ፅንስ አስወራጅ ሃኪም”፣ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በሆዷ የያዘችውን ፅንስ በማውጣት፣ ለአገልግሎቱ 300 ብር አስከፍሎ አሰናበታት፡፡ በወቅቱ የደረሰባትን የህመም ስሜት ስታስታውስ ግን አሁንም ድረስ ይዘገንናታል፡፡
‹‹ሰውነቴ ውስጥ ቀዝቃዛ ብረት ሲገባ ተሰማኝ። ህመሙ ጭንቅላቴ ድረስ የሚነዝር ነበር፡፡ ለደቂቃዎች ውስጤን ሲጎረጉር ከቆየ በኋላ በሃይል ብረቱን ሲያወጣው ራሴን ሳትኩ፡፡ ሆኖም ከዚህ ሁሉ ህመምና ስቃይ በላይ ፅንሱን መገላገሌ ለእኔ ትልቅ እረፍት ነበር፡፡ ድርጊቱ ግን በጤናዬ ላይ ጥሎ ያለፈው ችግር እንዳለ አምናለሁ፡፡ ወገቤና ማህፀኔ አካባቢ የሚሰማኝ የህመም ስሜት ችግር እንዳለብኝ ይጠቁመኛል፤ ተመርምሬ ሁኔታዬን ለማወቅ ግን የገንዘብ አቅሜ ይዞኛል፤ ከዕለት ጉርሴ ተርፎ ለህክምና እና ለምርመራ የማወጣው ገንዘብ የለኝም››
ይህን ያለችኝ በፓርኪንግ ሥራ ላይ ተሰማርታ ያገኘኋት ወጣት ነበረች፡፡ ወጣቷ ከሁለት ዓመታት በፊት በፈፀመችው ህገወጥ “ውርጃ” ሳቢያ ጤንነቷ አደጋ ላይ መውደቁን ታምናለች፡፡ የዚህችን ወጣት አይነት ታሪክ ያላቸው በርካታ ወጣቶች በህገወጥ “ውርጃ” ምክንያት በደረሰባቸው የጤና ችግር ለሞትና ለዕድሜ ልክ የአካል ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡
በከተማችን አዲስ አበባ ፅንስን ማስወረድ ከባድ ነገር አይደለም፡፡ ‹‹ጥርስን የመንቀል ያህል ቀላል ጉዳይ ነው›› ይላሉ፤ በሙያው ላይ ከተሰማሩ ፅንስ አስወራጆች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው የሚናገሩት ደላሎች፡፡ ‹‹አርጋዧ” የምትጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ትቻል እንጂ በሆዷ የያዘችውንና ሰው ለመሆን የሚጣጣረውን ፅንስ ከማህፀኗ መንጥቀው የሚያወጡ በርካታ “ፅንስ አውራጅ” ባለሙያዎች በከተማዋ ሞልተዋል፡፡ በባህላዊና ዘመናዊ መሳሪያዎች ተደራጅተው በየቦታው ባሰማሩአቸው ደላሎች እየተመለመሉ የሚመጡላቸውን ደንበኞች እየተቀበሉ የሚያስተናግዱ ባለስምና ስም የለሽ ክሊኒኮች እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ከቅርብ አመታት በፊት ሜሪ ስቶፕስ በተባለው የጤና ተቋም በስፋት ይሰጥ እንደነበር የሚነገርለት የፅንስ ማስወረድ ተግባር፤ ዛሬ በርካታ የከተማዋ ጤና ተቋማት የሚሳተፉበት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በከተማዋ አራቱም አቅጣጫዎች ቅርንጫፎቹን ከፍቶ ለደንበኞቹ የፅንስ ማስወረድ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ሜሪ ስቶፕስ፤ በወቅቱ ‹‹ቤቢ ስቶፕስ›› የሚል መጠሪያ እስከመቀዳጀት መድረሱን ከአመታት በፊት ለህትመት በበቃ አንድ መፅሄት ላይ ሰፍሯል፡፡
በፅንስ ማስወረድ ተግባር ላይ ለተሰማሩ ክሊኒኮች፣ ደንበኞችን በማቅረብ የካበተ ልምድ እንዳለው የሚናገረውና ስሙን ለመግለፅ ያልወደደ አንድ ወጣት፤‹‹ሥራው ህይወትን ከማጥፋት ይልቅ ህይወትን ማዳን ነው›› ሲል ይገልፀዋል፡፡ “ያለ ጥንቃቄ በተደረገ የአንዲት ቀን ስህተት ህይወቷን ለአደጋ ያጋለጠችን ሴት ከመርዳት በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ?” ሲል ይጠይቃል፡፡ እንደ ወጣቱ አገላለፅ፤ አብዛኛዎቹ ለውርጃ ተግባር ወደ ክሊኒኮቹ የሚሄዱት ወጣቶች ዕድሜያቸው ከ17-23 የሚሆኑና ተማሪዎች ናቸው፡፡ ወጣቶቹ ያልተፈለገ እርግዝና ሲገጥማቸው የሚወስዱት ብቸኛ አማራጭ ማስወረድ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ደላላው ወጣት በጣም የሚደግፈው ተግባር ነው፡፡ ‹‹ምን ማለትሽ ነው ነጠላ ዜማዋን ከምትለቅ ብታስፈነጥረው አይሻላትም!?›› ሲል እንደዘበት ይናገራል፡፡ አብዛኛዎቹ ወጣት ሴቶች ከፍቅር ጓደኞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ላላማቋረጥ፣ ከቤተሰቦቻቸው የሚደርስባቸውን ጫና በመፍራትና አባት ያልተቀበለውን ልጅ ላለማሳደግ ውርጃውን እንደሚመርጡም ወጣቱ ነግሮኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግንባር ቀደም ረዳታቸው በመሆን ውርጃን ከሚፈፅሙ ባለሙያዎች ጋር ወጣቶቹን በማገናኘት ኮሚሽኑን ይቀበላል፡፡ እንዲህ እንደ ወጣቱ ያሉ “አውራጅ” እና “አስወራጆቹን” በማገናኘት እንጀራቸውን በልተው የሚያድሩ በርካታ ‹‹ቀሽት›› ደላሎችን ከተማችን አቅፋ ይዛለች።
በከተማዋ በሚገኝ አንድ የግል ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሁለተኛ ዓመት የማኔጅመንት ተማሪ የሆነችው ወጣት፣ ከወራት በፊት ለገጠማት ያልተጠበቀና ያልተፈለገ እርግዝና የተገላገለችው በእዚሁ አገልግሎት ከሚታወቁ የጤና ተቋማት በአንደኛው መሆኑን ትናገራለች፡፡ እንደ ወጣቷ አገላለፅ፤ በፀዳ ሥፍራ፣ በፀዳ ባለሙያ ለተሰጣት የፅንስ ማስወረድ አገልግሎት 950 ብር ክፍያ ፈፅማለች፡፡
ከውርጃው በኋላ በሰውነቷ ውስጥ ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር ለመከላከል የሚያስችል መድሃኒት በባለሙያው ታዞለት ወስዳለች፡፡ የማስወረድ ተግባሩ ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል ለሃይለኛ የህመም ስሜት ቢዳርጋትም የከፋ የጤና ችግርና ሥቃይ እንዳላጋጠማት ነግራኛለች፡፡ ይህንን የህክምና ተቋም ያገኘችውም እርግዝናዋን ለማረጋገጥ ምርመራ አድርጋ ስትወጣ ባገኘችው ወጣት ደላላ አማካኝነት ነው፡፡ ወጣቷ ውርጃውን የፈፀመችበት ክሊኒክ በከተማዋ በስፋት የሚታወቅና በሌላ የጤና ህክምናዎች ስሙ የታወቀ ክሊኒክ መሆኑንም ጠቁማኛለች፡፡ ወጣቷ እንደምትለው፤ ተግባሩ በድብቅና በሽፍን ሲከናወን ለጤና አደገኛና አስፈሪ ይሆናል፡፡ በገሃድና በሥርዓት መከናወኑ በውርጃ ሰበብ ህይወታቸውን የሚያጡ በርካቶችን ለመታደግ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ለአገልግሎቱ የሚከፈለውን ክፍያ ተመጣጣኝ ያደርገዋል፡፡
በፅንስ ማስወረድ ተግባር ላይ ለተሰማሩ የጤና ተቋማት ደንበኞችን እያፈላለጉ የሚያቀርቡ ደላሎች ሥራ የሚበዛባቸው ወራት አሉ፡፡ መጋቢት፣ ግንቦትና ነሐሴ ውርጃ በስፋት የሚፈፀምባቸውና ደላሎቹ ጥሩ ገቢ የሚያገኙባቸው ወራቶች ናቸው፤ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከጥምቀትና ከሰርግ በዓላት ጋር በተያያዘ በርካታ ወጣቶች ‹‹ነፃነት›› የሚያገኙባቸውና ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ የሚፈፅሙባቸው ጊዜያት በመሆናቸው ነው፡፡ በክረምቱ ወራት ለዚህ ችግር የተጋለጠች ሴት፣ ጣጣዋን ጨርሳ ለመስከረም ት/ቤት ብቁ የምትሆነውም በነሃሴ ወር ላይ በመሆኑ ደላሎቹ ገቢያቸው እንደሚደራ ወጣቱ ደላላ አጫውቶኛል፡፡
በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ መሰረት፤ውርጃ መፈፀምም ሆነ ለዚህ ተግባር መተባበር ወንጀል ነው፡፡ የአገሪቱ ህግ ውርጃ ተግባራዊ ሊደረግበት የሚችልበትን ምክንያቶች በተሻሻለው የወንጀል ህጉ በግልፅ አስቀምጦታል፡፡ አንዲት ሴት ውርጃን መፈፀም የምትችልባቸውን ምክንያቶች ያሰፈረው ህጉ፤ ሴቲቱ ውርጃ ለመፈፀም የምትፈልግበትን ምክንያት እንድትገልፅ አትገደድም ሲል ውርጃን በግልፅ መፍቀዱንም መከልከሉንም የማያሳይ አንቀፅ አክሎበታል፡፡
Comment
There are no comments made yet.


There are no replies made for this post yet.
Be one of the first to reply to this post!