1. yoftahe samuel
  2. ወጎችና መጣጥፎች / Creative Articles
  3. Thursday, 08 June 2017
ጥቁር ሻማ
ዛሬም እንደወትሮዋ ማልዳ ነው ከአጎዛዋ ላይ የተነሳችው ያለፉትን ዘጠኝ ወራት በሙሉ የጠዋት ልማዶቿ ተዘበራርቀዋል፡፡ ያ መልከመልካም ፊቷ እንኳ የሞትን ጥላ እንደተሸከመ ነቅቶ ደስታ እንደራቀው ያድራል፡፡ ለራሷ መኖር አቁማለች ‹ከማይመሽ ቀን የማይነጋ ሌሊት ይሻላል› ማለት ታበዛለች፡፡ ረፋድ ሲሆን እንደሌላው ጊዜ ሁሉ ከለምለሙ ሳር ላይ ተቀመጠች ‹ፋሬስ› ብላ የጠራችውን ጨቅላ ልጇን ገላ በፍቅር ልትዳብስ፤ በድንገት ግን ኩርኩር ከምትለዋ ሬድዮ አንድ ቆየት ያለ ግን በየአመቱ የሚዜም ልዩ ስሜት ያለው ህብረ-ዜማ ወደ ጆሮዋ ይስረቀረቅ ጀመረ፤ እርሷም ትዝታ በጦሩ እንዳሻው እንዲያማስላት ፈቀደችለት፤ በሃያል ዝምታም ሙዚቃውን ተከትላ ወደ አንክሮዋ ተሰደደች፡፡
‹‹ያሳለፋችሁት ጊዜ የድካማችሁ ፍሬ ይኸው ብሩህ ሆኗል ………….
…………..እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን…….››
ከአንድ አመት በፊት……
የመመረቂያ ፅሁፏን ሃሳብ አማካሪዋ ስላልወደደው ለሰአታት ሃሳብ እያነሱ ሲጥሉ ነው የቆዩት፡ ድክምክም ብሏታል፡ በተሰበረ መንፈስ ለወራት የለፋችበትን ፕሮጀክት ታቅፋ ወደ ማደሪያ ክፍሏ አመራች ዶርሟ እንደገባችም ጓደኞቿ ባዘጋጁት የምስራች ውሃ አጥምቀው “surprise!” አሏት ፤ ዛሬ ከ22 አመት በፊት የተወለደችበት ዕለት ነው፡፡ ባልጠበቀችው መንገድ መወለዷን ስላበሰሯት በፕሮጀክቷ መበስበስ ለመናደድ ጊዜ አላገኘችም፡፡
ሁሉም ጓደኞቿ የእንኳን አደረሰሽ መልዕክታቸውን ካስተላለፉላት በሗላ ስለማታ ዕቅዳቸው ማውራት ጀመሩ በጊቢ ውስጥ የሚቆዩበት የመጨረሻ ዓመታቸው እንደመሆኑ ከአልኮል ውጪ ነፃ የሚያደርጋቸው ምሽት እንደማይኖር አምነዋል፡፡ በእነርሱ ቋንቋ ‘ፍርክርክስ’ ‘ቅንጥስጥስ’ ሊሉባት ነፋሻዋን ምሽት ቀጠሮ አስያዟት፡፡ ለፍቅር ጓደኛዋም ደውላለት ስለቀን ሁኔታዋና ስለምሽቱ ዕቅዳቸው በዝርዝር ዘገበችለት እርሱም ተስማማ፡፡ ከፍቅረኛዋ ጋር ብዙ ነገር አብረው አሳልፈዋል ያው! ሆድ ጦሙን እንዳያድር ጥቂት የማይባሉ ብርዳማ ሌሊቶችን በአንድ ገላ አብረው ሞቀዋል፤ እነርሱ እንደሚሉት በመሃከላቸው ያለው ፍቅር ምንም አይነት የመከላከያ ጥንቃቄ እንዳያደርጉ ያዛል፤ ምናልባት እንደሚባለው ፍቅር አይነ-ስውር ሆኖ ይሆን እንጃ ብቻ፡፡ ሰዓታት ካለፉ በሗላ ምሽቱ ደረሰ ያቺ ውብ ከሁለት ጓደኞቿና ከፍቅር አጋሯ ጋር ሆነው ጩኸት ከተሞላው ጨለማ ውስጥ ደስታቸውን ሊፈልጉ ቀጠሮአቸውን አክብረው እየተጣደፉ ወጡ…
መሸታ-ቤቱ በሰዎች ብዛት ተጨናንቋል፤ ድምፅ ማጉያው ታንቡሩን እየደለቀ ማዜሙን ተያይዟል፤ ባለ ልደቷ ጉብልም ከጓደኞቿ ጋር መዝናናቷን ቀጥላለች፡፡ ጭለማው እየገፋ ጩኸቱ እየበረታ ሄደ፡ ብርጭቆዎች ይንቋቋሉ፡ ሴት ልጅ ያለወጓ ያለልኳ ትጠጣለች አስረሽ ምቺዉ ከሯል ወጣቱ ሁሉ በአንድ ትርታ የሚጠቀም ይመስል አንድ እኩይ ባህሪ ያንፀባርቃል፡፡
ሌሊቱን አጋምሰው ወጡ፡፡ ቢሆንም ግን ወደ ጊቢ የሚወስድ ታክሲ አላገኙም አማራጭ ሲያጡ እየተወላገዱም ቢሆን በእግራቸው ለመሄድ ወሰኑ፡፡ ትንሽ እንደተጓዙ ከሗላቸው አንዲት ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ወደ እነርሱ መጣች፡፡ በውስጧ የነበረው ግን የሁለት ሰው ቦታ ስለነበር ሁለቱ ጓደኞቿን አሳፍረው ጥንዶቹ ያንን ብርዳማ ሌሊት በፍቅር ተቃቅፈው የስካር ወሬያቸውን እያወጉ ተጓዙ፡፡
የድቅድቁን ጨለማ መንገድ እንዳጋመሱ ግን ሶስት የሚሆኑ የመንደር ዱርዬዎች አጋጠሟቸው ጥንብዝ ብለው መስከራቸውን የተመለከቱት ጎረምሶችም መሻታቸውን ለመፈፀም ተጣደፉ በድንገት ግን የፍቅር አጋሯ ባረፈበት ከባድ ቡጢ ተንገዳግዶ ፊቱ ከነበረው የድንጋይ ጉብታ ላይ ተፈጠፈጠ፡ ዱርዬዎቹ አደጋ በማድረስና በመዝረፍ ብቻ አላበቁም የዛችን መልከመልካም ሴት ገላ በቀሚሷ አሻግረው ጎመዧት እንጂ፤ ጎምዥተውም ተጠጓት ተጠግተውም ተገናኟት ቦታው በደምና በነባዘር ጨቀየ፡፡ ከሰዓታት በሗላ በዚያ ሲያልፍ የነበረ የምሽቱ ተረኛ ጥበቃ በገጠመው ነገር እጅጉን አዝኖ አስፈላጊውን ሁሉ አደረገላቸው፡፡ ይህ ከሆነ ከሁለት ቀን በሗላ በአካባቢዋ ወዳለ ክሊኒክ በድን አካላቷን ይዛ ሄደች፡፡ የመረመራት ሀኪምም ወደ ቢሮው ጠርቶ ሁለት ዜናዎች እንዳሉት አሳወቃት፡፡ ‹ኧኧ… የሶስት ወር ቅሪት ነሽ› ብሎ ጥሩውን ዜና ጀመረ… አላስጨረሰችውም ክው ብላ ቀረች፡ የእናቷ የተስፋ ድምፅ፤ የአባቷ ‹‹አደራ ልጄ›› የሚለው ምክር፤ ዲግሪ የማግኘት ፅኑ ፍላጎቷ ሁሉም በቅፅበት በዓይነ-ህሊናዋ እየተደቀኑ ሰላም ነሷት ሁለተኛውን ዜና ለመስማት ትዕግስት አላገኘችም ተነስታ ወጣች ሀኪሙም የማህፀን ኢንፌክሽን እንዳጋጠማትና ቫይረሱ በደሟ ውስጥ እንደሚገኝ የሚያስረዳውን ወረቀት ከሌሎች ፋይሎች ጋር ደባለቀው፡፡ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ እንደበራው ሻማ ልትጠፋ አዲስአበባን ለቃ ወደ ገጠሪቷ ኢትዮጵያ ነጎደች፡፡
Comment
There are no comments made yet.


There are no replies made for this post yet.
Be one of the first to reply to this post!